አርባ ምንጭ፦ መጋቢት 5/2018 ዓ.ም (አርባምንጭ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን)
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ባለሀብቶች በጋሞ ዞን ለደረሰው አደጋ ለምግብ ፍጆታ የሚውል የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ አበርክተዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
አቶ ቦጋለ አክለውም ደግና ሩኅሩኅ በሆነው በጋሞ ሕዝብ ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ፣ አሁን የተደረገው የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መሆኑንና በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም በበኩላቸው በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፣ ለተጎጂዎች የሚሆን የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጋሞ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በችግር ወቅት በአካል ተገኝቶ ላሳየው ወገናዊ አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።
ዋና ተጠሪው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ ላደረገው የዓይነት ድጋፍና ላሳየው አጋርነት በዞኑ ሕዝብና በመንግሥት ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።









