የንግድ ሥርዓቱን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የንግዱን ማህበረሰብ ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ ።

አርባምንጭ ፥ ሀምሌ 16/2018 ዓ.ም
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በአርባምንጭ ከተማ ለንግዱ ማህበረሰብ በ”ዲጂታል ማርኬቲንግ እና ኢ-ኮሜርስ” ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ቦጋለ ቢታኔ የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የንግዱ ማህበረሰብ የዘመነና ስልጡን ሆኖ ወቅቱ በሚፈልገው የቴክኖሎጂ ስርአት ንግዱን በማዘመን እንዲሰራ አባላቱን ማብቃት ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ከጊዜው ጋር የዘመኑ የንግድ ማህበረሰቦችን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስልጠናው በሁሉም መዋቅሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቀጣይም እንደሚሰጥ አክለዋል።
በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ የንግዱ አካላት አቅማቸውን በየጊዜው በስልጠና ማሳደግ እንደሚገባና ያገኙትን ክህሎት ወደ መሬት ማውረድ እንደሚያስፈልግ አቶ ቦጋለ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሄለን ረታ እንደገለፁት፣ ምክር ቤቱ የንግዱ ማህበረሰብ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተዉን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር በትኩረት እየሰራ ነዉ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከክልል ምክር ቤቶች ጋር በመቀናጀት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የጠቀሱት ወ/ሮ ሄለን፣ በየክልሉ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአባላት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ተስፋ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በቢዝነስ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን አቅም በየጊዜው በስልጠና ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ መሬት ማውረድና መተግበር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ሀገሪቱን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ እሱባለው የንግዱን ማህበረሰብ በዲጂታል ተክኖሎጂ በማጠናከር ሀገሪቱን ተወዳዳሪ ማድረግ ከባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ረዳት ፕሮፌሰር ልሳነወርቅ አማረ በንግድና ዘርፍ ማህበራት የተደራጁ የምክር ቤቱ አባል በመሆን በተቀናጀና በተደራጀ የግሉን ዘርፍ ኢኮኖሚ ንግድና አገልግሎት ዘርፍ ማሳደግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ የንግዱን ማህበረሰብ አቅም ማጎልበት የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድ ልዉዉጥ በዲጂታል ሥርዓት ተደራሽ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ረዳት ፕሮፌሰር ልሳነወርቅ ገልጸዋል።
ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም
አርባምንጭ




