ቅርንጫፎቻቸው ሀብት ለመሰብሰብ ሲባል ቀበሌና መንደር ስር የወረዱ፣ ከብዙሀኑ ሀብት ሰብስበው ለጥቂቱ የሚያሰራጩ ብዙሀኑ ገንዘቡን ሲጠይቃቸው ለማግኘት የሚቸገርባቸው የባንክ ሴክተሮች አሉን። የንግዱን ማህበረሰብ ሀብት አሟጠው ተጠቅመውበት በዝቅተኛ ወለድ ሲያደኸዩት እንጂ ሲጠቅሙት አላስተዋልንም። በብር የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያት የንግዱ ማህበረሰብ ገንዘብ እለት እለት እየወደቀበት የሚረዳው ባንክ አጥተን ተቸግረናል። ከዘመነው ባንክ ይልቅ እቁብን ምርጫው ለማድረግ የተገደደ የንግድ ማህበረሰብ እጅግ ብዙ ነው።
አሁን የንግዱን ማህበረሰብ ፍላጎት የሚያሟላ ባንክ ፍለጋ ላይ እንገኛለን!ከሚተባበር ባንክ ጋር እንተባበራለን።የጋራ ተጠቃሚነት እንጂ የተናጥል ተጠቃሚነት ሚዛኑ ሊታረም ይገባል።በአንድ ወገን ያደላ ጥቅም ረብ የለሽና ዘላቂነት የጎደለው ትብብር መሆኑን ባለፉት አመታት ለመገንዘብ ችለናል።
ብዙሀኑን መደገፍ የሚፈልግ ማንኛውም ባንክ በትብብር መንፈስ ለመስራት ከመጣ አብረነው እንሰራለን! በተግባርም እየተገማገምን የንግዱን ማህበረሰብ ከሚጠቅም የፋይናንስ ተቋም ጋር እየተጋገዝን በአብሮ የማደግ መንፈስ እናድጋለን!
ከዚህ ቀደም ይህንን ልምድ በከተማ ደረጃ ሞክረነው ተሳክቶልናል! ከዳሽን ባንክ ጋር ተደራሽነቱንና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ብዙ ሰርተን ለውጡን አይተናል።የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ለማህበረሰቡ በአርባምንጭና በጋሞ ዞን ላይ አሰራጭቶ የላቀ ተቀባይነትን አግኝቶ በብዙ አትርፏል።
አሁንም ለባንኮች እድል ሰጥተናል።ዛሬ #አሐዱ #ባንክ ጋር ከክልሉ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል።” ከብዙሀን ለብዙሀኑ” በሚል መለያው የሚታወቀው አሐዱ ባንክ ቃሉን በተግባር ሊያሳይ ጉዞውን ጀምሯል።ከኛ የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን ልንጠይቅ ዝግጁ ነን።
ውጤቱን አብረን እናያለን!
ታህሳስ 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ






