(የካቲት 13፤2018፤ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ)
የደቡብ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶ ከአዲስ አበባ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ጋር አብሮ መስራት በሚያስችላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ስራዎች ዙሪያ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡ ፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ቻምበር ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ ናቸው፡ ፡
የደቡብ ኢት/ያ ንግድ ም/ቤት ፕሬዝደንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ ከአዲስ ቻምበር ጋር በጋራ ለመሥራት በመቻላቸው ደስታ እንደተስማቸው ገልጸው ንግድ ም/ቤታቸው አባላቱ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሲንቀሳቀሱ በንግድ ዙሪያ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ከአንጋፋው ንግድ ም/ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ጋር በመተባብር ለመፍታት ስምምነቱ በእጅጉ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡በክልሉ ያሉ ብዝሀ ሀብቶች ወደመሀል አዲስ አበባና ከሀገር ውጪ በላቀ ሁኔታ እሴት ተጨምሮባቸው የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የአዲስ ቻምበር ያለውን አለም አቀፍ ቅርበት እና ተሰሚነት ወደክልላችን በማውረድ ለንግዱ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በጋራ መስራት የዚህ ስምምነት ዋነኛ ግብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአዲስ ቻምበር ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ የፊርማ ሥነሥርዓት ላይ የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ ንግድ ም/ቤታቸው ያካበተውን ሰፊ ተሞክሮ ለክልሉ ንግድ ም/ቤት ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የንግዱ ሕ/ሰብን በገበያና በንግድ መረጃ በማስተሳሰር እንዲሁም በጋራ የፖሊሲ አድቮከሲ ሥራዎች ዙሪያ አዲስ ቻምበር ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ያግዛል ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል በእርሻና በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ሰፊ የገበያ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ አስታውሰው አዲስ ቻምበር በሚያዘጋጃቸው የንግድ ማስፋፊያ ኹነቶች ላይ የክልሉ ነጋዴዎችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚደርግ ገልጸዋል ፡፡
ሁለቱ ም/ቤቶች በጋራ ለመሥራት ከተስማሙባቸው ሌሎች ነጥቦች መካከል አቅም ግንባታ፤የንግድ ድጋፍ አገልገፍሎት፤ በዲጂታልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፤ በንግድ ማስፋፊያና ፕሮሞሽን ዘርፎች የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
የአለም አቀፉ ንግድ ምክር ቤት አባል የሆነው አዲስ ቻምበር በሀገር ውስጥ እና በውጪ ካሉ በርካታ ከተሞችና ክልሎች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለው የጋራ ስምምነት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡ ፡
Via@ www.southethiopiachambers.com









