በኢትዮጵያ የ1፣ የ5 እና የ10 ብር ኖቶች ከገበያ እየጠፉ መምጣታቸው ተራ የቴክኒክ ችግር ሳይሆን፣ በኢኮኖሚው የታችኛው እርከን ላይ የሚገኘው ማኅበረሰብ የገንዘብ አቅም መፈራረሱን የሚያሳይ "ቀይ ማስጠንቀቂያ" መሆኑን ታዋቂው ኢኮኖሚስት ክቡር ገና ገለጹ።
ኢኮኖሚስቱ ይህንን አስተያየት የሰጡት፣ የትናንሽ የገንዘብ ኖቶች መጥፋት ትርጉም ምን እንደሆነ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
እንደ ክቡር ገና ትንታኔ፣ የገንዘብ ኖቶች በአጋጣሚ አይጠፉም። ይልቁንም በዋጋ ንረት ግፊት ከዕለት ተዕለት ሕይወት ይገፋሉ። የሸቀጦች ዋጋ ከሰዎች ገቢ በበለጠ ፍጥነት ሲያድግ፣ ትናንሽ ኖቶች ትርጉም ያለው ነገር መግዛት ያቆማሉ።
"ኖቶቹን ማንም አይግዳቸውም (ግድ አይሰጥቸውም)፣ ማንም መግለጫ አያወጣባቸውም፤ ነገር ግን በቀላል ሁኔታ ዝውውራቸው ይቆማል" ያሉት ክቡር ገና፣ ይህ ሁኔታ ኢንፍሌሽን ለዓይን እንዲታይ የሚያደርግበት መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ሻጮች ዋጋን ወደ ላይ ይጠቀልላሉ (Rounding up)፣ ገዢዎችም መልስ አይጠብቁም። ይህ ደግሞ በድሆች ትከሻ ላይ የሚጫን፣ ማንም ያልመረጠውና ማንም የማያመልጠው "ስውር ግብር" ነው ብለውታል።
የትንሽ ገንዘቦች መጥፋት ከኢኮኖሚ ባለፈ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል ያሉት ኢኮኖሚስቱ፣ የሚከተሉትን ሦስት አደጋዎች ጠቁመዋል፦
1. ገንዘብ በትናንሽ የዋጋ ልዩነቶች መካከል ያለውን ልዩነት መግለጽ ሲያቅተው፣ ገበያው ርኅራኄ የሌለውና ድርድር የማይታይበት ይሆናል።
2. በገንዘብ ላይ ያለው እምነት መላላት። ሰዎች የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ሲወርድ ሲያዩ፣ ከማስቀመጥ ይልቅ ወዲያውኑ ለማውጣት ይቸኩላሉ። ይህ "ለመትረፍ የማሰብ" ስነ-ልቦና ኢኮኖሚውን ይበልጥ ያናጋዋል።
3. ኢ-ፍትሐዊነት መዋቅራዊ መሆኑ። ሀብትና ባንክ ቤት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ከዋጋ ንረት ሲከላከሉ፣ ምንም የሌላቸው ግን በዋጋ መጠቅለል እና በአገልግሎት ክፍያዎች ይጎዳሉ።
ብዙዎች የኤሌክትሮኒክ ክፍያ መፍትሔ እንደሆነ ቢሞግቱም፣ ክቡር ገና ግን የዲጂታል ክፍያ የዋጋ ንረቱን ከመፈወስ ይልቅ ችግሩን "የማይታይ" እንደሚያደርገው ይከራከራሉ። ዲጂታል ክፍያዎች የዋጋ ለውጦችን የሚያፋጥኑ እና በትናንሽ ግብይቶች ላይ ተጨማሪ ክፍያዎችን በመጫን ድሃውን የሚቀጡ ናቸው ብለዋል።
"ትንሽ ገንዘብ ሲጠፋ፣ ማኅበረሰቡ የሚሰጠው መልዕክት 'ትናንሽ ሕይወቶችና ትናንሽ ትርፎች ከእንግዲህ ዋጋ የላቸውም' የሚል ነው፤ ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ውድቀት ብቻ ሳይሆን የሞራል ውድቀትም ጭምር ነው" ሲሉ ክቡር ገና አስጠንቅቀዋል።
መንግሥትና የፖሊሲ አውጪዎች የሚከተሉትን እርምጃዎች እንዲወስዱ አሳስበዋል። የዋጋ ንረትን በንግግር ሳይሆን በእውነት መጋፈጥ፣ የታችኛው ማኅበረሰብ ገቢ ከዋጋ ንረት ጋር እንዲመጣጠን ማድረግ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ትናንሽ ግብይቶችን የሚከላከል እንጂ የማይቀጣ እንዲሆን ማድረግ።
ጽሁፋቸውን ያገባደዱትም "የትናንሽ ኖቶች መሞት ጉዳቱ ወደ ላይኛው እርከን እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ትልልቆቹ ኖቶች (100 እና 200 ብር) ራሳቸው ዛሬ በዝምታ ጫና ውስጥ ናቸው። ይህ ካልተገታ፣ ነገ ትልልቆቹ ኖቶችም እንደ ትልቅ መቆጠር ያቆማሉ" በሚል ነው።




